የማጅራት ገትር

                                 የማጅራት ገትር በሽታ

የማጅራት ገትር በሽታ በተለያዩ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን የሚመጣ ፤ በአግባቡና በቶሎ  ካልታከመ ለሞት እና ለተለያዩ ጠንቆች የሚዳርግ ህመም ነው። ይህ ህመም ሜኒንጅስ (meninges) የተባሉትን የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ስስ ሽፋን በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን መጠቃት ተከትሎ የሚከሰት ችግር ነው።

ባክቴሪያ ፣ ቫይረስ፣ ፈንገስ፣ፓራሳይት እና የጭንቅላት ካንሰር የማጅራት ገትር በሽታ በማምጣት ይታወቃሉ።በዚህ ክፍል በዋናነት በባክቴሪያ ምክንያት ስለሚከሰተው የማጅራት ገትር በሽታ እናያለን፡፡

የማጅራት ገትር በሽታ አጋላጭ ምክንያቶች የሚከተሉትን ያካትታል።

  • ጨቅላ እድሜ ወይም የእድሜ መግፋት (ከ5 አመት በታች ወይም ከ60 ዓመት በላይ)
  • የስኳር በሽታ ፣ ሥር የሰደደ የኩላሊት ድካም ፣ የአድሬናል ሆርሞኖች እጥረት ፣ ሃይፖፓራታይሮይዲዝም ወይም ሲስቲክ ፋይብሮሲስ (cysticfibrosis)
  • የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም (የ ኤች አይ ቪ ኤድስ)
  • ተፋፍጎ መኖር (በወታደራዊ ካምፕ እና በኮሌጅ ዶርም ) ፣ ይህ አኗኗር የሜኒንጎኮካል ገትር በሽታ ወረርሽኝ አደጋን ይጨምራል።
  • የአልኮል ሱሰኝነት
  • የደም ሥር (V) የአደንዛዥ ዕፅ አላግባብ መጠቀም

               የማጅራት ገትር በሽታ ምልክቶች

የማጅራት ገትር በሽታ በርካታ ምልክቶች ያሉት ሲሆን ተከታዮቹ ሶስት ምልክቶች ግን አይነተኛ የማጅራት ገትር በሽታ ምልክቶች ናቸው።

  • ራስ ምታት
  • ትኩሳት
  • የአንገት ህመም (የማጅራት መገተር)

ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆኑት ባክቴሪያ ወለድ የማጅራት ገትር በሽታ ያላቸው ሰዎች ከአራቱ የማጅራት ገትር በሽታ ምልክቶች ማለትም ራስ ምታት ፣ትኩሳት፣ የአንገት ህመም እና ንቃተ ህሊና መቀነስ ዉስጥ ቢያንስ ሁለቱ ይኖራቸዋል።

ከባድ የሚባሉት የማጅራት በሽታ ጠንቆች የሚከተሉትን ያካትታል፦

  • የመስማት ችሎታ መቀነስ
  • የእይታ መስተጓጎል (የኮርቲካል ዓይነ ስውርነት)
  • የራስ ቅል ነርቭ መስተጓጎል
  • ሽባነት
  • አታክሲያ (ሚዛን አለመጠበቅ)
  • የመጣል በሽታ
  • የአእምሮ ዘገምተኝነት እና የትኩረት ማጣት
  • ሃይድሮሴፋለስ ((የጭንቅላት ፈሳሽ መብዛት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *