የጨጓራ ባክቴሪያ
የጨጓራ ባክቴሪያ
የጨጓራ ባክቴሪያ በተለይ በታዳጊ ሀገሮች በጣም የተለመደ ችግር ነው። ይህ ባክቴሪያ የጨጓራ ቁስለት በማምጣት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው።ይህ ባክቴሪያ ሄሊኮባክተር ፓይሎሪ (helicobacter pylori) ወይም በአጭሩ ኤች ፓይሎሪ(H.pylori) ይባላል። ከግራም ኔጋቲቭ ባክቴሪያዎች የሚመደብ ሲሆን በቅርጹ ኮኮባሲለስ (coco-bacillus) ይህ ባክቴሪያ በጨጓራ ውስጥ የመኖር ልዩ ችሎታ የተጎናጸፈ ነው። በዚህም የጨጓራን አሲዳማ ከባቢ ተቋቁሞ ይኖራል። ከዚህ አልፎ ተርፎም የሚኖርበትን ሌሎች የባክቴሪያ በሽታዎችን የመከላከል አቅም አለው። ለምሳሌ የታይፎይድ ጨጓራ ይጎዳል። በነገራችን ላይ የጨጓራ አሲድ (ሃይድሮክሎሪክ አሲድ-HC) በሽታን በከፊል ይከላከላል።
የጨጓራ ባክቴሪያ (ኤች ፓይሎሪ) በተበከለ ምግብ ወይም መጠጥ ወደ ተጠቂው ሰው ይገባል። ወደ ጨጓራ ከገባ በኋላ አመቺ ቦታ ላይ ይቀመጣል። ከባቢው ዙሪያ ያለን አሲድ የሚያመክን ንጥረ ነገር ያመርታል። በዚህም በቀላሉ ለመራባት እና ጨጓራ ላይ ጉዳት ለማድረስ ይችላል።
የጨጓራ ባክቴሪያ ምልክቶች
አብዛኛው የጨጓራ ባክቴሪያ ያለባቸው ሰዎች ምንም አይነት ምልክት አይኖራቸውም።
የጨጓራ ቁስለት ካስከተለ የተለያዩ ምልክቶች ያሳያል።እነርሱም፦
- የሆድ (ከእምብርት በላይ) ህመም በተለይ የማቃጠል ስሜት
- ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና ከምግብ በኋላ መጨናነቅ ስሜቶች የርሀብ ስሜት ሲኖር ይብሳሉ (ይህም ቁስለቱ- ዶድነም (duodenum) ላይ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል) ።
- የደም ማስታወክ እና ማስቀመጥ
- ከፍተኛ የሆድ ቁርጠት እንዲሁም የማያቋርጥ ትውከት
- ከፍተኛ የሆነ የሰውነት መክሳትን ያስከትላል።
