ታይፎይድ ፊቨር (ታይፎይድ)
ታይፎይድ ፊቨር (ታይፎይድ)
ኢትዮጵያ ውስጥ ስመ ገናና ከሆኑ በሽታዎች ዉስጥ አንዱ የታይፎይድ በሽታ ነው፡፡ ታይፎይድ (typhoid) የህክምና ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ታይፈስ መሳይ ማለት ነው፡፡ይህም ምልክቶቹ ከታይፈስ ጋር ስለሚመሳሰል ነው። እንዲሁም ኢንተሪክ ፊቨር (Enteric fever) እየተባለ በህክምናው ባለሙያዎች ይጠራል፡፡ ታይፎይድ ሳልሞኔላ (salmonella) በተባለ የባክቴሪያ ተህዋስ የሚመጣ ፤ካልታከመ ለሞት
ሊዳርግ የሚችል በሽታ ነው፡፡
የታይፎይድ በሽታ ምልክቶች
ታይፎይድ አምጪ ጀርሙ (ሳልሞኔላ) ወደ ሰዉነት ከገባ 7 እስከ 14 ቀናት በኋላ የታይፎይድ ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ።
- ትኩሳት ዋነኛ የታይፎይድ ምልክት ነው።የትኩሳቱ ባህሪ በየቀኑ እየጨመረ የሚሄድ (stepwise ወይም step ladder) ነው።
- የሆድ ህመም እና የሆድ ድርቀትን ያመጣል። አንዳንዶች ላይ ተቅማጥ ያስከትላል።
- ሳይታከም ከቆየ ደረቅ ሳል፣ራስ ምታት፣ የአእምሮ ንቃት መቀነስን አልፎ ተርፎም ራስን እስከ መሳት ሊያደርስ ይችላል።
የታይፎይድ በሽታ ጠንቆች
የታይፎይድ ህመም ሳይታከም ከቀረ ወይም በአግባቡ ካልታከመ አያሌ ጠንቆችን ሊያስከትል ይችላል።ከእነዚህም ዉስጥ የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው።
- የማጅራት ገትር በሽታ
- የአንጀት መሸንቆር (bowel perforation and peritonitis )
- የአእምሮ መዛባት (psychosis )
- የመገጣጠሚያ ቁስለት
- የአጥንት ቁስለት (osteomyelitis )
ከታይፎይድ በሽታ ጋር የሚመሳሰሉ በሽታዎች ታይፎይድ ከብዙ በሽታዎች ጋር ይመሳሰላል። የተወሰኑትን ለመጥቀስ:- ወባ፣ካላዛር፣ ትርፍ አንጀት፣አሜባ፣ታይፈስ፣ብሩሴሎሲስ እና ደንጊ ይገኙበታል።
